#ጉዞ_በፀሎት(አቃቂ እና ቦሌ)
፡
፡
#ክፍል_አስራ_አምስት፡
፡
#በዘሪሁን_ገመቹ_ዋቤ፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧
‹‹ለማንኛውም ተመልሼ መጣለሁ..ና ወደቢሮ እንመለስ …››ብለው ሰለሞንን አስከትለው ወደቢሯቸው ተመለሱ፡፡
‹‹በል አሁን ንገረኝ ልጄ እንዴት ናት?››
‹‹እኔ እንጃ እንዴት እንደሆነች አለውቅም?››
‹‹ማለት ደብዳቤውን ስትሰጥህ አይተሀት የለ..?ከስታለች…እንዴት ነች ተጎሳቁላለች?ልቧስ እንዴት ነው…?ታውቃለህ አይደል የልብ በሽተኛ ነች››
‹‹ደብዳቤውን በአካል መጥታ አይደለም የሰጠችኝ..ማለቴ ቢሮዬ በሚገኝበት ህንፃ መታጠቢያ ቤት አስቀምጣ ስልክ ደወለችና እንድወስድ አዘዘችኝ..ስልኬን ከየት እንዳገኘች አላውቅም…ሁሉን ነገር የተነጋገርነው በስልክ ነው…በወላጆቼ ትዳር መካከል አለመግባባት አለና እርዳቸው ብላ መቶ ሺ ብር በደብተሬ አስገብታለች….መልሼ ስልኳን ብደውልላት አይሰራም…እራሴ ስፈልግህ መልሼ አገኝሀለው ነው ያለችኝ..እኔ የማውቀው ይሄኑን ነው፡፡››
ኪሱ ገባና ቢዝነስ ካርዱን አውጥቶ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠ‹‹ይሄው አድረሻዬ …ቢሮዬ ሜኪሲኮ ኬኬር ህንፃ ላይ ነው….ዝግጁ ስትሆኑ ደውሉልኝ….ካልሆነም ይንገሩኝ ገንዘቡን ተመላሽ አደርጋለው፡፡አሁን ልሂድ፡፡››
‹‹እሺ በቃ…አመሰግናለው..አሁን ተረጋግቼ ማሰብ አለብኝ..ደውልልሀለው፣ልጆቹ ይሸኙሀል››አሉት፡፡
እሱም ሌላ ምንም ተጨማሪ ቃላት ሳይናገር ቦርሳውን ያዘና ሹልክ ብሎ ወጥቶ ሄደ፡፡
በሁለተኛው ቀን የሚጠብቀው ቁጥር ተደወለ…የልብ ምቱ ፍጥነት እንደጨመረ እየታወቀው ነው…እንደምንም ለመረጋጋት ሞከረና አነሳው፡፡
‹‹አቤት …..››
‹‹ሃይለ ልኡል ነኝ….››
‹‹አወቅኮት፣ ሰላም ኖት ?››
‹‹ደህና ነኝ….እቤት ብቅ ብትል ይመችሀል?››ሰከን ባለና በተረጋጋ የድምፅ ቅላፄ ጠየቁት፡፡
‹‹መቼ…አሁን››
‹‹አዎ አሁን ብትመጣና ..በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ብናወራ ደስ ይለኛል››
‹‹እሺ….ከአንድ ሰዓት በኃላ እደርሳለሁ..››
‹‹አመሰግናለሁ….ከባለቤቴ ጋ ሆነን እንጠብቅሀለን››
‹‹ጥሩ በቃ መጣሁ….››ስልኩን ዘጋና ቀጥታ ቦርሳውን ይዞ ከመቀመጫው ተነሳ….ወደፊት ለፊተኛው ክፍል ሲገባ ለሊሴ ፊትለፊቷ ያለውን ኮምፒተር ከፍታ አፍጥጣ ነበር….
‹‹ልወጣ ነው…ዘሬ ተመልሼ የምመጣ አይመስለኝም››
‹‹እሺ በቃ..ባለጉዳይ ከመጣ…ለነገ ቀጠሮ ይዤላቸዋለው››አለችው፡፡
‹‹ጥሩ እንደዛ አድርጊ….መልካም ውሎ››ብሏት ቢሮውን ሙሉ በሙሉ ለቆ ወጣ፡፡
መኪናውን እራሱ እያሽከረከረ….አእምሮውም በሀሳብ እየተሸከረከረ ቀጥታ ወደአቶ ኃይል ልኡል ቤት ነዳው…ምን እንደሚጠብቀው አያውቅም..እርግጥ ና ብለው ሲጠሩት በጣም በተረጋጋ እና በተለሳለሰ ድምፅ ነው…ግን ያንን ያደረጉት ሁሉ ነገር ሰላም ነው ብሎ በማመን በገዛ እጁ ሄዶ እጅ እንዲሰጣቸው አስበው ከሆነስ? ይሄ የእቅዳቸው አንዱ አካል ቢሆንስ?››እራሱን ደጋግሞ ጠየቀ…በሀሳብ ከመብሰልሰል ለደቂቃ እንኳን ሳያነጥብ ሰፈራቸው ደረሰ …መኪናውን ከሩቅ አቆመና ደወለ፣ስልኩ ተነሳ››
‹‹ኪያ እንዴት ነሽ?››
‹‹ሰልም ነኝ….አንተስ?››
‹‹አለው…እዛ የነገርኩሽ ቦታ ጠርተውኝ እየሄድኩ ነው››
‹‹የት?››
‹‹አንቺ ደግሞ …የጠፋችው ልጅ ወላጆች ጋር ነዋ››
‹‹ና ብለው ጠሩህ?››
‹‹አባትዬው አሁን ጠርተውኝ በራፋቸው ጋር ደርሼ ወደውስጥ ዘልቄ ከመግባቴ በፊት መኪናዬን አቁሜ ነው የምደውልልሽ››
‹‹ምነው ፈራህ እንዴ?››
‹‹አይ ለምን ፈራለሁ….ማለቴ ከገባሁ በኃላ በፀጥታ ከእነሱ ጋር ለመነጋገር ስልኬን ስለማጠፋ ድንገት ደውለሽ ስልኬ ካልሰራልሽ እንዳታስቢ ብዬ ነው››
‹‹አይ ጥሩ አደረክ…ለማንኛውም እንደወጣህ ደውልልኝ››
‹‹እሺ….ኪያ …ቸው››ስልኩን ዘጋ፡፡ቀለል አለው፡፡‹‹ቢያንስ አሁን እዛው በገባሁበት ከቀረሁ በቀላሉ አድርሻዬን ታገኘዋለች፡፡››ብሎ አሰበና መኪናውን አንቀሳቀሰ….የውጭ በራፍ ጋር ደረሰና ክላክሱን አንጣረረ….ወዲያው በራፉ ተከፈተና…ጠብደል ጥቁር ሱፍ የለበሰ ጠባቂ ወደእሱ መጣና …ማንነቱን ጠየቀው‹‹አዎ አንተን እየጠበቁሀ ነው››ብሎት መልሶ ሄደና በራሀፍን ከፈተለት ….ወደውስጥ ዘልቆ ገባና ከአራት መኪና በላይ ወደቆመበት ገራዥ በመሄድ ክፍት ቦታ ፈልጎ መኪናውን አቆመና ሞተሩን አጥፍቶ ወረደ…..ጠባቂው እየመራ ሳሎን በራፍ ድረስ ወሰደውና ወደኃላ ተመለሰ…
እራሳቸው አቶ ኃይለልኡል ነበሩ በራፍ ድረስ መጥተው በወዳጅነት አቀባበል አቅፈው የተቀበሉት….ወደሳሎን ይዘውት ዘለቁ…መጀመሪያ ምግብ እንብላ…‹‹እስከአሁን ቁርስ ሳንበላ እየጠበቅንህ ነው››አሉት፡፡
‹‹ዝም ብላችሁ ተቸገራችሁ….እኔ እኮ በልቼ ነበር የመጣሁት››
‹‹ቢሆንም…ና ቁጭ በል….››ቀድመው ተቀመጡና የሚቀመጥበትን ቦታ አሳዩት…ተቀመጠ
‹‹ልጇች..ስንዱን ጥሯት››
ሰራተኞቹ ግራ የገባቸው ይመስል ዝም ብለው ሰውዬው ላይ አፈጠጡ፡፡
‹‹ምን አፍጥጣችሁ ታዩኛላችሁ…ክፍሏ ነች…አንዳችሁ ሂዱና እንግዳው መጥቷል ነይ በሏት…የተቀራችሁ ቁርሱን አቅርቡ››
ሁሉም ትዛዙን ሰምተው ተበታተኑ
‹‹እንዴት ነው …ወ.ሮ ስንዱ ተሸላቸው?፡፡››ሰለሞን ጠየቀ፡፡
‹‹አዎ…እድሜ ላንተ የልጃችንን ሰላም መሆን ዜና ካሰማሀን በኃላ ተሸሏታል…የተሳሰረ የነበረ እግሯቾም ታምራዊ በሆነ ፍጥነት ተላቀውላት አሁን በራሷ መራመድ ችላለች፡፡››
‹‹በእውነት በጣም እስደሳች ዜና ነው…ያልኳችሁን ስላመናችሁኝ ደስ ብሎኛል››
‹‹አይ እሱ እንኳን በቀላሉ አላመንህም…ስላአንተ ለሁለት ቀን ሳስጠና ነበር…በዛ ላይ ከእሷ ጋር የተደዋወላችሁትን የስልክ ልውውጥ አግኝቼ አዳምጬዋለው…የልጄን ድምፅ ሰምቼያለው…በሰላምና በጤና መኖሯን ያረጋገጥኩት ከዛ በኃላ ነው…በቀላሉ ላምንህ
ሳላልቻልኩ ይቅርታ….ደግነቱ እንዲህ በቀላሉ እንደማላምንህ ልጄ አስቀድማ ነግራሀለች…ይገርማል ይሄን ያህል ጠልቃ ምታውቀኝ አይመስለኝም ነበር››
‹‹ልጆት አይደለች…ልጆች እኮ ወላጆች የሚያደርጉትን እያንደንዱን ድርጊት በጥልቀት ያስተውላሉ ፣በአእምሮቸውም ይመዘግባሉ…ስለወላጆቻቸው በጥልቀት ነው የሚያውቁት››
‹‹ትክክል ነህ ..››ንግግራቸውን በወ.ሮ ስንዱ መምጣት ምክንያት አቆረጡ….ሰሎሞን ከመቀመጫው ተነስቶ በትህትና ሰላምታ ተቀበላቸው….ወንበር ስበው ተቀመጡ..ቁርስ ቀረበ….ጠረጴዛው ሙሉ ቢሆንም ያን ያህል አፒታይት የነበረው ሰው አልነበረም….ቁርሱ እንደተጠናቀቀ ከወንበራቸውን ተነስተው አንደኛ ፎቅ ላይ ወደሚገኘው የአቶ ኃይለልኡል ቢሮ ተያይዘው ሄዱ.. ወደሶፋው ሄዱና ተቀመጡ..፡፡
‹‹እንግዲህ አሁን መነጋገር እንችላለን››አቶ ኃይለልኡል ጀመሩ
ወ.ሮ ስንዱ ተቀበሏቸው‹‹ልጄ እንደው አባክ እርዳን ..ልጃችን ወደቤቷ እንድትመለስ አሳምናት››ከመቀመጫቸው ተነስተው እግሩ ላይ ሊደፉ ሲሉ በአየር ላይ ትከሻቸውን ያዘና መልሶ አስቀመጣቸው፡፡
‹‹አይገባም..እኔ እዚህ ያለሁት እኮ ልረዳችሁ ነው..የእኔም ምኞትና ፍላጎት ያ ነው››
‹‹እኮ አድርገዋ….ያለችበትን እንድትነግርህ አሳምናት›››
‹‹አይ በእንደዛ አይነት ሁኔታ እንኳን ምትስማማ አይመስለኝም..እሷ ወደቤቷ ምትመለስበትን አንድና ብቸኛ መንገድ በግልጽ ተናግራለች…ምንም አይነት ችግር ሳይፈጠር ደስተኛ ሆና ወደቤቷ እንድትመለሰ ያለችውን አድርጎ ማሳየት ብቻ ነው ያለብን፡፡››
‹‹ይሄውልህ ልጄ…ልጃችን ያለችውን ለማድረግ እኔም ባለቤቴም ተስማምተናል…..ለዛ ቃል እንገባለን..አንተ ትረዳናለህ እኛም በመሀከላችን ያለውን ችግር እንፈታዋለን..››