" በቴ ምን ያህል ለህዝቡ አስፈላጊ እንደነበር በህዝቡ ሁኔታ፣ በህዝቡ ለቅሶ ተመልክቻለሁ ! " - የፖለቲከኛ አቶ በቴ ኡርጌሳ ባለቤት
ከወራት በፊት መቂ ላይ በግፍ የተገደሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራር ፖለቲከኛው አቶ በቴ ኡርጌሳ ባለቤት ከልጆቻቸው ጋር ከሀገር ወጥተው አሜሪካ መግባታቸው ተሰምቷል።
ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ አንበሴ በአጭር ቪድዮ ባሰራጩት ቃላቸው ፥ አሁን ላይ ከልጆቻቸው ጋር አሜሪካ ሀገር እንደሚገኙ ገልጸዋል።
" ባለቤቴ በቴ ኡርጌሳ ከሞተ 7ኛ ወር ሊሞላ ነው። " ብለዋል።
" በዓለም ላይ ያላችሁ ሃዘናችንን የተካፈላችሁ ፣ የኦሮሞ ኮሚውኒቲ ፤ በቴ ምን ያህል ለህዝቡ አስፈላጊ እንዳሆነ በሃዘናችሁ ፤ ባለው ነገር ሁሉ አይተናል " ሲሉ ገልጸዋል።
" እሱ ካረፈበት ቀን ጀምሮ በሀዘናችን ያለቀሳችሁ፣ ከኛ ጋር ያዘናችሁ ፣ በገንዘባችሁ በሃሳባችሁ በጸሎታችሁ የረዳችሁን እግዚአብሔር ይስጥልን ፤ እናመሰግናለን " ብለዋል።
" የኛን ሰላም መሆን ለተጨነቃችሁ ፤ ድምጻችን ሲጠፋ ለተጨነቃችሁ ' ምን ሆናችሁ ነው ? ' ላላችሁን ያለንበትን ለመግለፅ ነው ፤ አሁን ያለነው አሜሪካ ነው ፤ በሰላም ደርሰናል " ሲሉ ገልጸዋል።
" ኤምባሲዎች በጣም እናመሰግናለን ፤ ያለንበት ቦታ ድምጻችን የጠፋባችሁ ስልካችን እንቢ ያላችሁ ፣ ቤታችን ድረስ ሄዳችሁ ያጣችሁን ምን ሆናችሁ ነው ? ላለችሁን ላደረጋችሁልን ነገር ሁሉ እናመሰግናለን " ብለዋል።
" በቴ ምን ያህል ለህዝቡ አስፈላጊ እንደነበር በህዝቡ ሁኔታ፣ ለቅሶ ተመልክቻለሁ " ያሉት ወ/ሮ ስንታየሁ " እኔ እውነት ለመናገር በቴ ከሞተ በኃላ ነው ህዝቡ እንዴት በቴን ያውቅ እንደነበር የተረዳሁት ምክንያቱም በቴን እንደዚህ አላውቀውም ነበር እውነቱን ለመናገር ከጫፍ ጫፍ ነው ህዝቡ ያዘነው " ሲሉ በእምባ ታጅበው ስሜታቸውን ገልጸዋል።
እምባቸውን
😭 እያፈሰሱ የተናገሩት የበቴ ባለቤት " እሱ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም የዓለም ሰው እንደሆነ አውቃለሁ " ብለዋል።
አሁንም ከጎናቸው ሆነው በብዙ ነገር እየረዷቸው ላሉ በተለይ ለኦሮሞ ኮሚውኒቲ ፣ በውጭ ሆነው በስልክ እየደወሉ እያፅናኗቸው ያሉ፣ በፀሎታቸው ፣ በገንዘብ እየደገፏቸው ላሉ ሁሉ " እግዚአብሔር ይስጥልን " ሲሉ አመስግነዋል።
ወ/ሮ ስንታየው አንበሴ ፤ ልጆቻቸው ደህንነታቸው የተጠበቀ ቦታ ላይ እንዳሉና ትምህርትም እንደጀመሩ ገልጸዋል።
ወደፊት ጊዜው ሲደርስ ደግሞ ስላሳለፉት ነገር እንደሚገልጹ ቃል ገብተዋል።
ለተደረገላቸው ነገር ሁሉ እያነቡ በልጆቻቸው ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የ4 ልጆች አባቱ ፖለቲከኛው በቴ ኡርጌሳ ከወራት በፊት መቂ ላይ በግፍ መገደላቸው ይታወሳል። ከዛ በኃላ " ማጣራት ተደርጎ ስለ ግድያው ዝርዝር ማብራሪያ ለህዝቡ ይሰጣል " ተብሎ ቃል ቢገባም እስከ ዛሬ ስለ ግድያው ሁኔታ ፣ ከግድያው ጋር በተያያዘ ተጠያቂ ስለሆነ አካል በይፋ አንድም የተባለ ነገር የለም።
የፖለቲከኛ አቶ በቴ ኡርጌሳ ጉዳይ " ቄሱም ዝም መፅሃፉም ዝም " እንዲሉ ሆኖ ቀጥሏል።
#TikvahEthiopia
@tikvahethiopia