" በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስኳር በሽታ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ከ800 ሚሊዮን በልጠዋል " - ጥናት
° " አገራት ጤናማ አመጋገብን እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የሚደግፉ ፖሊሲዎችን ማውጣት አለባቸው " ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም
ከ1990 ጀምሮ የስኳር ታማሚዎች ቁጥር በአራት እጥፍ በመጨመር በአለም ከ800 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በስኳር በሽታ መያዛቸውን የአለም ጤና ድርጅት ያወጣው አዲስ ጥናት አመለከተ።
ጥናቱ ይፋ የተደረገው የዓለም የስኳር በሽታ ቀን በትላንትናው እለት በተከበረ ቀን ነው።
ጥናቱ የተሰራው የአለም ጤና ድርጅት ከ NCD Risk Factor Collaboration (NCD-RisC) ጋር በመተባበር ሲሆን ከ1,500 ተመራማሪዎች እና ባለሙያዎችን አሳትፏል።
ከ18 አመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ 140 ሚሊዮን ሰዎችን መረጃ በመተንተን የተሰራው ይህ ጥናት የስኳር በሽታ የስርጭት መጠን እና የህክምና ሽፋን ላይ ትኩረቱን በማድረግ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
በዚህም በ1990 እና 2022 መካከል ባለው ጊዜ የስኳር ህመም ከ7 ወደ 14 በመቶ መጨመሩን ያመለከተው ጥናቱ የስኳር ህመም መጠኑ እየጨመረ፤ የህክምና ተደራሽነቱም ዝቅተኛ እየሆነ መምጣቱን አሳይቷል።
አፍሪካ ደቡብ-ምስራቅ እስያ እና ምስራቅ ሜዲትራኒያን ዝቅተኛው የስኳር በሽታ ህክምና ሽፋን ያላቸው አህጉራት እንደሆኑ ተመላክቷል።
በ2022፣ ዕድሜያቸው 30 እና ከዚያ በላይ የሆኑ 450 ሚሊዮን የሚጠጉ አዋቂ የስኳር ህመምተኞች ውስጥ 59 በመቶው የስኳር በሽታ ህክምና እንደማያገኙ ጥናቱ አመላክቷል።
ይህ ቁጥር በ1990 ከነበሩት በስኳር ተይዘው የማይታከሙ ታማሚዎች ጋር ሲተያይ በ3.5 ጭማሪ ያሳየ መሆኑ ነው የተገለፀው።
ከስኳር በሽታ ተማሚዎች ውስጥ ዘጠና በመቶው ያልታከሙ አዋቂዎች የሚገኙት ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ነው ተብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም " ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ውስጥ የስኳር በሽታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አይተናል " ብለዋል።
በሽታው የተስፋፋው ከመጠን ባለፈ ውፍረት፣ ጤናማ ባልሆነ አመጋገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለማድረግ እንደሆነ ሲገልፁ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ደግሞ የበሽታውን ሁኔታ እንዳባባሱት ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ " ዓለም አቀፉን የስኳር በሽታ ለመቆጣጠር አገራት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለባቸው " ሲሉም አሳስበዋል።
አክለውም አገራት ጤናማ አመጋገብን እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የሚደግፉ ፖሊሲዎችን በማውጣት እና በሽታን በመከላከል እና በመቆጣጠር የበቃ የጤና ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
@tikvahethmagazine