View in Telegram
የሰውነት አካል ልገሳ ጉዳይ በኢትዮጵያ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ʺሰዎች ኩላሊታችንን ግዙን እያሉ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እንደሚመጡ ተገለጸʺ በሚል የሚሰራጨው ዜና ሀሰት እና ኮሌጃችንን  የማይመለክት ነው ብሏል፡፡ ኮሌጁ ʺሰዎች ኩላሊት ግዙን ብለው ወደ ማእከሉ ይመጣሉʺ የሚለው አባባል  ፍጹም ከእውነት የራቀ መሆኑ መታወቅ አለበት ሲል አሳውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ህግ የሰውነት ክፍልን በፈቃደኝነት ስለመለገስ ምን ይላል? ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጠበቃ እና የህግ አማካሪ የሆኑትን አቶ ዳንኤል ፈቃዱን አነጋግሯል። ጥያቄ:-የሰውነት ክፍልን በፈቃደኝነት ስለመለገስ የኢትዮጵያ ህግ ምን ይላል? አቶ ዳንኤል:- "የኢትዮጵያ ህግ እንደሚደነግገው እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያም እንደሚያመላክተው የሰውነት አካልን በፈቃደኝነት መለገስ በዘመዳሞች መካከል ብቻ ይፈቀዳል" ብለዋል። ነገር ግን በህጉ መሰረት በዘመዳሞች መካከል የሚደረግን የሰውነት አካል ልገሳ ምንም አይነት የገንዘብ ውል እንዳይኖረው ክልከላ የሚያስቀምጥ ሲሆን ገንዘብን እንደ ውል በማስቀመጥ የሚደረግ ልገሳን ህገ ወጥ መሆኑን ተናግረዋል ። ጥያቄ:- የሰውነት አካልን በፈቃደኝነት ለመለገስ መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምን ምን ናቸው። አቶ ዳንኤል:- ህጉ አስገዳጅ ነገሮች ብሎ ካስቀመጣቸው በዘመዳሞች መካከል ብቻ ፣ያለ ምንም ክፍያ እና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ገልጸው ከሦስቱ አንዱ ከጎደለ ልገሳው ተቀባይነት እንደማይኖረው ተናግረዋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የምግብ፣ መድኃኒት እና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ደንብ 299/2006 እንደሚያስቀምጠው የሰውነት አካልን በፈቃደኝነት ዝምድና ለሌለው አካል ለመለገስ በመሀከል ምንም አይነት የጥቅም ግንኙነት አለመኖሩን መረጋገጥ እንዳለበት እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል ። ይህንን የሚያረጋግጥ ራሱን የቻለ ተቋም መኖሩን ጠቁመዋል ። ጥያቄ :- ከላይ ከተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች ውጪ የሰውነት ክፍሉን በሽያጭ ያቀረበን አካል ህጉ ምን አይነት ቅጣት ያስቀምጣል? አቶ ዳንኤል:- ህጉ በሦስት መንገድ የሚያየው መሆኑን ተናግረዋል። - አስተዳደራዊ እርምጃ -የወንጀል ተጠያቂነት -የፍትሃብሔር ተጠያቂነት በ 1997 በወጣው በኢፌዲሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 573 ላይ እንደተቀመጠው በህጉ ከተቀመጠው ውጪ ይህንን ድርጊት የፈጸመ ከሆነ:- በተቋሙ ላይ አስተዳደራዊ ቅጣት እንደሚጣል የሚያስቀምጥ ሲሆን ይህም ፈቃድን መንጠቅ ሊሆን ይችላል። ለጋሹ በህይወት ያለ ከሆነ ከ 3-5 ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት እና የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል ይላል። ወሳጁ ሐኪም የአካል ክፍሉን ከሞተ አካል የወሰደ ከሆነ ከ 5 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ያስቀምጣል ። ወሳጁ ሐኪም የአካል ክፍሉን በህይወት ካለ ሰው በህጉ ከተቀመጠው ውጪ ከወሰደ ከ 5-10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ አስቀምጧል። በማጭበርበር ፣በማስገደድ ወይም በማታለል ጉዳዩ የሚመለከተው ሰው ሳይፈቅድ አካል ክፍል የወሰደ ከሆነ ከ 10-25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ አስረድተዋል። የፍትሀብሔር ተጠያቂነትን በሚመለከት የሰውነት አካል ልገሳ ያደረገ ሰው ልገሳውን በማከናወኑ የደረሰበት ጉዳት ካለ ለፍርድ ቤት በሚያቀርበው ክስ መሰረት ጉዳቱ በሚመለከተው አካል ተረጋግጦ የሚገባውን ካሳ የሚያገኝበት አሰራር መሆኑን የህግ ባለሞያው ተናግረዋል። #ምስል: ከዚህ ዜና ጋር የተያያዘው ምስል በሰው ሰራሽ አስተውሎት (Generative AI) አማካኝነት የተሰራ ነው። @tikvahethmagazine
Telegram Center
Telegram Center
Channel