ባሳለፍነው ሩብ ዓመት በአዲስ አበባ 107 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል ተብሏል።
ሁሉም የደንብ ጥሰቶች የትራፊክ አደጋን የሚያስከትሉ ቢሆኑም ዋና ዋና በሚባሉ የትራፊክ አደጋ መንስኤዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየተሰራ መሆኑን በአዲስ አበባ ፖሊስ የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የትራፊክ ሞያ እና ህዝብ ግንዛቤ ዲቪዥን ሃላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን አዳነ
ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
ሃላፊው በ2017 ሩብ ዓመት 612 ሺ 445 ግለሰቦች በትራፊክ ደንብ ጥሰት ምክንያት ለቅጣት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥ:-
° መንጃ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲያሽከረክሩ የተገኙ 306
° ሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ ይዘው ሲያሽከረክሩ የተገኙ 213
° ቀይ የትራፊክ መብራት የጣሱ 45 ሺ
° የደህንነት ቀበቶ ሳያስሩ ያሽከረከሩ 24 ሺ
° የእጅ ስልክ እያዋሩ ሲያሽከረክሩ የተገኙ 28 ሺ
° አመታዊ የቴክኒክ ምርመራ ሳያከናውኑ ሲያሽከረክሩ የተገኙ 6,671
° ከፍጥነት ወሰን በላይ ሲያሽከረከሩ የተገኙ 7,316 ሰዎች ይገኙበታል።
ጠጥቶ ማሽከርከርን በሚመለከት ለ28 ሺ አሽከርካሪዎች ምርመራ ተደርጎ 871 ዱ በህግ ከተቀመጠው በላይ ጠጥተው የተገኙ በመሆናቸው ምክንያት እንዲቀጡ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
በሩብ አመቱ 107 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን በ 2016 ሩብ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 106 ሰዎች ህይወታቸው አልፎ ነበር።
ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር 379 ሲሆን በ 2016 ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 385 ሰዎች ጋር ሲነጻጸር መቀነስ ታይቶበታል።
በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት በአንጻሩ ከፍተኛ ጭማሪን ያሳየ ሲሆን በሩብ ዓመቱ 8,953 ንብረቶች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ባሳለፍነው ሩብ ዓመት ካጋጠመው 8,253 የንብረት ጉዳት ጋር ሲነጻጸር በ 700 ብልጫ ያለው ነው።
በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በገንዘብ አልተተመነም።
የተሽከርካሪ መለያ፣ መመርመሪያ እና መመዝገቢያ አዋጅ 681/2002 መሰረት ማንኛውም ተሽከርካሪ በዓመት አንድ ጊዜ የተሽከርካሪ የምርመራ ሂደትን አልፎ በመንገድ ላይ መንቀሳቀስ እንዳለበት ቢደነግግም በሩብ ዓመቱ ከ 6 ሺ በላይ ተሽከርካሪዎች ይህንን ሳይፈጽሙ በመንገድ ላይ መገኘታቸውን ኃላፊው አክለው ገልጸዋል።
@tikvahethmagazine