Смотреть в Telegram
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#ሳህለወርቅ_ዘውዴ “ አቅጣጫዬን አሳይቻለሁ፤ በዛ መሠረት ለመስራት ሞክሬአለሁ ” - የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዜዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበጎ ፈቃድ የተሰባሰቡ ሴቶችና የሴት መሪ ድርጅቶች በጋራ በመሆን በቅርቡ የሥራ ዘመናቸውን ላጠናቀቁት ለቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሸራተን አዲስ ሆቴል ዛሬ የምስጋና ፕሮግራም አዘጋጅተው ነበር። በዚሁ መርሀ ግብር አቶ አባዱላ ገመዳ፣ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ፣ የሴቶች ማኀበራት መሪዎችና በሌሎች የሥራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ ሴቶች ተገኝተዋል። ፕሮግራሙ ከተዘጋጀበት ዓላማ አኳያም ለቀድሞ ፕሬዜዳንቷ “ በጣም ውድ ” እና “ ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ” የተባለለት የሀገር ቅርስ ጭምር የተቀረጸበት የስዕል ስጦታ የተበረከተላቸው ሲሆን፣ “ ከሚገባው ቦታ አስቀምጠዋለሁ ” በማለት ስጦታውን ላበረከቱላቸው ምስጋና አቅርበዋል። በመርሀ ግብሩ ባደረጉት ንግግር ደግሞ፣ “ የዛሬ 6 ዓመት ገደማ ያደረኩት ንግግር የ18 ደቂቃ ነበር። ጥቂት ጊዜ ነው የነበረኝ ለመዘጋጀት። የደረሰብኝም አልገባኝም ነበር ” ሲሉ አስተውሰዋል የቀድሞ ፕሬዜዳንቷ። “ ሴቶች የሚለውን ቃል 29 ጊዜ፣ ሰላም የሚውን ቃል 30 ጊዜ ተናግሬ ነበር ” ያሉት ሳህለወርቅ፣ “ ለራሴ አልዋሽም፣ ለሌላም አልዋሽም። አቅጣጫዬን አሳይቻለሁ፣ በዛ መሠረት ለመስራት ሞክሬአለሁ ” ሲሉም አክለዋል። “ ተያይዘን መስራት አለብን። ጡረታ የሚባለውን ነገር አሁን ነው የጀመርኩት ግን እረፍት የለም። ጡረታም ተወጥቶ እንደማይታረፍ የቀደሙኝ እያሳዩኝ ነው። ላደረጋችሁልኝ በጣም ነው የማመሰግነው ” ነው ያሉት። የቀድሞዋ ፕሬዜዳንት ከዚህ ቀደም፣ “ ‘የሰው ልጅ ሆዱ ሲከፋው ጊዜም እንደ ሰው ሲገፋው፣ መሄጃ መውጫ ሲጠፋው ዝምታ ብቻ ነው ተስፋው’ ይላል ማህሙድ ‘ዝምታ ነው መልሴ’ን ሲያዜም ” ብለው፣ “ አንድ ዓመት ሞከርኩ ” የሚል ፅሑፍ በX (ቲዊተር) ገጻቸው አጋርተው ነበር። በወቅቱም ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ይህንን ምስጢር አዘል የሆነ ፅሑፋቸውን በተመለከተ ግን ዛሬም የሰጡት ማብራሪያ የለም። የቀድሞዋ ፕሬዜዳንት ሳልለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ ሴት የኢትዮጵያ ፕሬዜዳንት ሆነው ለ6 ዓመታት 4ኛ የኢትዮጵያ ፕሬዜዳንት ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው፣ የሥልጣን ዘመናቸው በመጠናቀቁ ኃላፊነታቸውን ለፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ማስረከባቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። #TikvahEthiopiaFamilyAA @tikvahethiopia
Telegram Center
Telegram Center
Канал